ሳይከፈት የተነበበው የ300 ዓመቱ ደብዳቤ

Image name: Sealed letter.jpg

ተመራማሪዎች ለ300 ዓመታት ያክል ሳይከፈት ተጠቅልሎ የተቀመጠን ደብዳቤ ቨርቹዋል አንፎልዲንግ ሲሉ በሰየሙት መንገድ ደብዳቤውን ሳይከፍቱ በውስጡ ያለውን ይዘት ማንበባቸው ተነገረ፡፡ ‹‹የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ›› እንደሚባለው ታሪክን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት እሙን ነው፡፡ ቅርሶች በሚጠኑበትም ሆነ እንክብካቤ በሚደረግላቸው ጊዜ ታሪካዊና ቅርሳዊ ይዘታቸውን በማይጎዳ መሆን ይገባዋል፡፡ በተለይ እንደ እኛ ባለች የታሪክ መዝገብ በሆነች ሀገር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ቅርሶችን ከንክኪ ጠብቆ ለማጥናት ይህ መንገድ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡
ይህ አለማቀፍ የተመራማሪዎች ቡድን በጥንት የአውሮፓ ዘመን የተጻፈውን የታሸገ ደብዳቤ ሳይከፍት የተለያዩ ኮምፒውተራዊ ስልቶችን በመጠቀም በውስጡ የያዘውን መልዕክት ማንበብ ችሏል፡፡ ይህ በኔቸር ኮሚኒኬሽን ታትሞ የወጣውና በመረጃ ምንጫችን SciTechDaily የተዘገበው መረጃ እንደሚያመለክተው MIT ቤተ-መጽሐፍትና የኮምፒውተርና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ትብብር የተሰራና ይፋ የሆነ ነው፡፡ ቨርቱዋል አንፎልዲንግ የተባለው ስልትም ኤክስ ሬይ ማይክሮቶሞግራፊን በመጠቀም የተሰራ ነው፡፡
ሌተርሎኪንግ ወይም ደብዳቤን በሚስጥራዊ መንገድ አሽጎ መላክ በጥንታዊው የሀገራት ስርዓት ውስጥ በጣም የተለመደ ነው፡፡ በዚህ ደብዳቤውን ሳይከፍቱ በማንበብ ሒደት የቅርስ ጥበቃ ሙያተኞች፣ ታሪክ አዋቂዎች፣ ኢንጅነሮች፣ የምስል ሙያተኞችና ሌሎች ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ በዚህም የብዙዎች መተባበርና በጋራ መስራት ትልልቅ የሚባሉ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል መሆኑን መረዳታቸውን ከተመራማሪዎቹ አንዱ ተናግረዋል፡፡
ያልተከፈተን ደብዳቤ ማንበብ የሚያስችለውን ስልተ ቀመር ያበለጸጉት ኤማንዳ ጋሻይ እና ሆሊ ጃክሰን የተባሉ በኤልክትሪካል ኢንጅነሪንግና ኮምፒውተር ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የሚሰሩ ተማሪ ተመራማሪዎች ናቸው፡፡ በዚህ ስልተ ቀመር በመጠቀም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሐምሌ 31፣ 1697 የተጻፈ የአንድ ደብዳቤን ይዘት ማንበብ ችለዋል፡፡ 




© SciTechDaily