“እንደ አገር ሳንጠፋ እስካሁን መኖር የቻልነው አገሪቷ የተሠራችበት ድርና ማግ እምነትና ኃይማኖት ስለሆነ ነው” – አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ


የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ መከራ እና ፍዳ እያየ ያልጠፋነውና እስካሁን መኖር የቻልነው አገሪቷ እንደ አገር የተሰራችበት ድርና ማግ እምነትና ኃይማኖት በመሆኑ ነው ሲሉ አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ አስታወቁ ። በትውልድ ግንባታ ሂደት ውስጥ ከ30 ዓመት በፊት የነበረው ትውልድ በምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ፣ ለምን ብሎ የሚጠይቅ፣ ኢትዮጵያዊ እሴቱን አክብሮ የሚይዝ እንደሆነ አመለከቱ።
አገልጋይ ዮናታን በሀገራዊ ትውልድ ግንባታ ዙሪያ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት ፣ ኢትዮጵያ ዝም ብሎ የተሰራች ሀገር አይደለችም ፡፡ አገሪቱ የተሰራችው ረጅም ዓመት በወሰደ የእምነትና ኃይማኖት ድርና ማግ ነው ፡፡
በአገሪቱ እንደነበረውና እንዳለው ችግር እና ጥያቄ ፤ እንደ አንዳንድ የውጪ ጠላቶቻችን ናፍቆት ቢሆን ኖሮ እስካሁን ተበትነን ነበር የሚሉት አገልጋይ ዮናታን፣ በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን ሁሉ መከራ እና ፍዳ እያየ ያልጠፋነውና እስካሁን መኖር የቻልነው አገሪቷ እንደ አገር የተሰራችው በእምነትና በኃይማኖት ድርና ማግ ስለሆነ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በጠንካራ የእምነት መሰረት ላይ የተገነባች አገር ነች ፡፡ አብዛኛው የፖለቲካ እሳቤዎቻችን የፍትሐብሄር፣ የማህበራዊ ፣ የሽምግልና፣ የእርቅ እሴቶቿ መሰረት የሚያደርጉት ኃይማኖት ነው፡፡ በአገር ግንባታ ላይ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ሙስሊሙም በእስልምና ክርስቲያኑም በክርስትና አስተምህሮዎቻቸው ትልልቅ አስተዋጽዖዎችን አድርገዋል ብለዋል፡፡
ከጊዜ በኋላ የመጡ የኃይማኖት ተቋማት ከአንዳንድ መሰረታዊ ከሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ሊወጡ ይገባል ፣ የአገር ግንባታ ሂደት አይመለከታቸውም የሚሉ ያልተገባ እሳቤዎች መምጣታቸውን የሚናገሩት አገልጋይ ዮናታን፤ ከዚህ የተነሳም ስለፖለቲካ እና ስለአንዳንድ ሀገራዊ ጉዳዮች ስትናገሪ ‹‹አንተ ኃይማኖተኛ አይደለህም እንዴ፤ እዚህ ውስጥ አትግባ›› የሚል ነገር እየተደመጠ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡