askwala.com - ካንሰር የማይደፍራቸው እንስሳት
Header







ካንሰር የማይደፍራቸው እንስሳት


አሳ ነባሪ፣ ዶልፊን እና ፖርፔሶች ካንሰርን የመቋቋም ብቃታቸው ከኛ ከሰው ልጆች በእጅጉ የላቀ ነው፤ አሁን ላይ ታድያ ተመራማሪዎች የዚህን ምክንያት ለማወቅ የተቃረቡ መስሏል፡፡
እነዚህ የሲቴሻ ዝርያ እንስሳት ከሰው ልጆች አንፃር እጅግ የረዘመ ዕድሜን የሚኖሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ አሳ ነባሪዎች እስከ 200 ዓመታት ዕድሜን መኖር ይችላሉ፡፡ ይህ ታድያ ሰውነታቸው ግዙፍ እንደመሆኑና ብዙ ሕዋሳትን በውስጡ እንደመያዙ ረጅም ዕድሜ የመኖራቸውን ነገር ምስጢራዊ ያደርገዋል፡፡ የቺሊው ኡሰትራል ዲ ቺሊ ዩኒቨርሲቲ ምሁሯ ዳንኤላ ታአዳ-ማርቲኔዝ በሰውነታችን ያሉት የሕዋሳት ቁጥር በበዛ ልክ ከነዚህ ሕዋሳት መካከል አንደኛው በካንሰር የመጠቃቱ እድል እያደገ እንደሚመጣ ትናገራለች፡፡ በዚህም አካል በገዘፈና ዕድሜም በረዘመ ቁጥር በሺዎች ወይም ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህዋሳት አደገኛ እየሆኑ እንደሚመጡ ታስረዳለች፡፡ ግን ደግሞ የሲቴሻ እንስሳት ከዚህ በተቃረነ መልኩ ከሰው ልጆችም ሆነ ሌሎች አጥቢ እንስሰሳት በላይ ለካንሰር ያላቸው ተጋላጭነት አነስተኛ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ፔቶስ ፓራዶክስ ተብሎ ይታወቃል፤ እንስሳቱ በዝግመተ-ለውጥ አማካኝነት የተሻለ የካንሰር መከላከያ ስልትን ማዳበር ችለዋል፡፡
ሆኖም ይህን እንዴት ሊያሳኩት ቻሉ የሚለው ጥያቄ መመርመር ነበረበት፡፡ አሁን ላይ ዳንኤላ ታአዳ-ማርቲኔዝ እና ባልደረባዎቿ 1077 የቲዩመር ሰፕረሽን ጂን/በራሂዎችን (TSGs) ዝግመተ-ለውጥን መርምረዋል፡፡ የእነዚህን በራሒዎች ዝግመተ-ለውጥን ሰባት የሲቴሻ ዝርያ እንስሳትን ጨምሮ ከ15 የአጥቢ እንስሳት ዝርያዎች ጋር አነፃፅረውታል፡፡ ከሲቴሻ ዝርያዎቹ መካከል የዘረ-መል ብልሽት፣ የቲዩመሮችን ስርጭት እና በሽታ መከላከያ ስርዓትን የሚቆጣጠሩ በራሒዎች በተመራማሪዎቹ ተለይተው እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ በተጨማሪም የጥናት ቡድኑ የሲቴሻ ዝርያዎቹ ከሌሎች አጥቢ እንስሳት በ2.4 እጥፍ በበለጠ የቲዩመር ሰፕረሽን በራሂዎችንችን የሚያገኙ እና የሚያጡ መሆናቸውን ለመረዳት ችሏል፡፡
ታድያ ተመራማሪዎቹ የአሳ ነባሪዎችን በራሒ ወስደን የሰው ልጆች ውስጥ በማኖር ካንሰርን እንከላከል ባይሉም የቲዩመር ሰፕረሽን ሚናን መጫወት የሚችሉ በራሒዎችን ከሌሎች እንስሳት ላይ ፈልጎ ማግኘትና ይህን እንዴት እንደሚከውኑ ማወቅ ከተቻለ ምናልባትም ከዚህ ሂደት ጋር በተመሳሰለ መልኩ ለካንሰር ህክምና የሚሰጥ መድሃኒትን መስራት ያስችል እንደሆን ይናገራሉ፡፡ 




© New scientist   













Short info

× Chat