askwala.com - ከአንድ ቢሊዮን ዓመታት በኋላ ምድር ኦክስጅኗን ትነጠቃለች
Header







ከአንድ ቢሊዮን ዓመታት በኋላ ምድር ኦክስጅኗን ትነጠቃለች

Image name: earth.jpg

ምድራችን ከአንድ ቢሊዮን ዓመታት በኋላ ሕይወትን ለማኖር በማይቻል ሁኔታ ኦክስጅን አጠር እንደምትሆን አዲስ ጥናት አሳየ፡፡ ዛሬ ላይ ኦክስጅን ከምድራችን ከባቢ አየር ውስጥ የ21 በመቶውን ድርሻ በመያዙ እንደ ሰው ልጅ ላሉ ይህ ጋዝ ለሚያስፈልጋቸው ፍጥረታት መኖርያ ምቹ አድርጓታል፡፡ ሆኖም በቀደመው የምድራችን ታሪክ ከባቢ አየር ውስጥ ይገኝ የነበረው የኦክስጅን መጠን ዝቅተኛ የነበረ ሲሆን አሁንም በድጋሚም መልሶ የመውረዱ ዕድል ከፍተኛ ነው፡፡
የጃፓኑ ቶሆ ዩኒቨርሲቲ ምሁር ካዙሚ ኦዛኪ እና የአሜሪካኑ ጆርጂያ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ አጋራቸው ክሪስ ራይንሀርድ የምድራችንን አየር ንብረት፣ ስነ-ሕይወት እና ስነ-ምድር መረጃን በግብዓትነት በመጠቀም ከባቢ አየሯ ወደፊት ምን ያህል ለውጦችን እንደሚያስተናግድ ትንበያዊ ትንተናን ሰርተዋል፡፡ እናም አጥኚዎቹ ምድራችን ለቀጣዮቹ አንድ ቢሊዮን ዓመታት ከፍተኛ የኦክስጅን መጠንን እንደያዘች የምትቀጥል ቢሆንም ከዚያ በኋላ ግን የኦክስጅን መጠኑ በፍጥነት አሽቆልቁሉ ከዛሬ 2.4 ቢሊዮን ዓመታት በፊት ወደነበረበት ዝቅተኛ መጠን እንደሚመለስ ተናግረዋል፡፡
ለዚህ ለውጥ ዋናው መነሻ ፀሐይ እያረጀች በሄደች ቁጥር ይበልጥ እየሞቀች እና የምትለቀው ኃይልም ከፍ እያየለ መሄዱ ነው፡፡
በአጥኚዎቹ ስሌት መሰረት ይህ ሁኔታ በምድራችን ከባቢ አየር ውስጥ የሚገኘውን ካርበን ዳይ ኦክሳይድ ሙቀት እንዲሰበስብ እና በኋላም እንዲሰባበር ስለሚያደርገው የካርበን ዳይ ኦክሳይድ ይዘቱ እንዲመናመን ያደርገዋል፡፡ ያለ በቂ ካርበን ዳይ ኦክሳይድ ደግሞ እፅዋትን ጨምሮ የፎቶሲንተሲስ ስራን የሚያከውኑ አካላት ለመቆየት እና ኦክስጅንን ለማምረት የማይቻላቸው ይሆናል፡፡ እነዚህ አካላት የኦክስጅን ዋነኛ ምንጭ እንደመሆናቸው ደግሞ የእነርሱ አለመኖር የኦክስጅን አለመኖርን ያስከትላል፡፡ ይህም ታድያ አሁን ላይ በምድራችን ካለው የኦክስጅን መጠን በአንድ ሚሊዮን እጥፍ ያነሰ ኦክስጅን ብቻ እንዲቀር እንደሚያደርግ ክሪስ ራይንሀርድ ይናገራል፡፡
ለውጡ አንዴ ከጀመረ በኋላ ምድራችን ኦክስጅኗን በ10 ሺህ ዓመታት ልዩነት ውስጥ ብቻ የምታጣው ይሆናል፡፡ በዚህ ፍጥነት የሚደረግ ለውጥ ደግሞ ፍጥረታት ከሚቋቋሙት በላይ ስለሚሆን ደቂቀ አካላት ዳግም ዘውዳቸውን ጭነው የምደራችን ብቸኛ ኗሪና ገዢ ሲሆኑ የተቀረነው ፍጥረታት ግን ከነዋሪዎች ዝርዝር እንደምንሰረዝ የአጥኚዎቹ ግምት ነው፡፡ የኡዞን መሳሳቱ ከፍተኛ የሆነ የፀሐይ ጨረር እና ሙቀትን በመላው ምድራችን ላይ ስለሚያሰፍን ከየብስ ፍጥረታት ባሻገር ኑሯቸውን በውሃ ውስጥ ያደረጉትም ተመሳሳይ እጣ ይደርሳቸዋል፡፡
ከኦክስጅን ቅናሽ በተጨማሪ በከባቢ አየራችን የሚገኘው የሚቴን መጠን በ10 ሺህ እጥፍ እንደሚያድግም የተመራማሪዎቹ ትንበያ ያሳያል፡፡
በሌላ መልኩ ጥናቱ የሌላው ዓለም ፍጥረታትን ለማግኘት በሚደረገው አሰሳ ላይ ጠቃሚ ግብዓት ናቸው ያላቸው ምክረ-ሐሳቦችንም ጠቁሟል፡፡ 




© New scientist   













Short info

× Chat