askwala.com - በኮቪድ-19 የተጠቁ ህፃናት ድንገተኛ የኩላሊት ተግባር መስተጓጎል ሊያጋጥማቸው ይችላል
Header







በኮቪድ-19 የተጠቁ ህፃናት ድንገተኛ የኩላሊት ተግባር መስተጓጎል ሊያጋጥማቸው ይችላል


ኮቪድ-19 አልያም MIS-Cን (Multisystem Inflammatory Syndrome) ተከትሎ ሆስፒታል ገብተው ከሚታከሙ ህፃናት መካከል 10 በመቶ ያህሉ ድንገተኛ የኩላሊት ተግባር መስተጓጎል (Acute kidney injury) እንደሚያጋጥማቸው አዲስ ጥናት አስታወቀ፡፡ የኩላሊት ጉዳቱ ያጋጠማቸው ህፃናት ሌሎች የወረርሺኙ ተጠቂ ህፃናት በሆስፒታሉ ከሚቆዩበት ጊዜ በአማካኝ ከስምንት ቀናት በላይ በሆስፒታሉ ይቆያሉም ተብሏል፡፡ ታድያ ሁኔታው በባለሙያዎቹ ዘንድ አሳሳቢ ሆኗል፡፡
ድንገተኛ የኩላሊት ተግባር መስተጓጎል ያለባቸው ሰዎች የሰውነትን ፈሳሽ በመቆጣተር ረገድም ሆነ እንደተለመደው ሽንታቸውን ለመሽናት አዳጋች ሊሆንባቸው ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ ጉዳቱ እራሱን የሚያክም ቢሆንም አንዳንዴ ግን ኩላሊቶችን ከጥቅም ውጪ እስከማድረግ ወደሚደርስ ጉዳት ሊሸጋገር እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ኮቪድ-19ኝን በተመለከተ ከህፃናት አንፃር በሽታው ኩላሊት ላይ የሚያመጣው ተፅዕንዖ በአዋቂዎች ዘንድ እንደተደረገው በስፋት ሳይጠና ቀርቷል፡፡ በዚህም መነሻነት ነው አጥኚዎቹ ኮቪድ-19ኝም ሆነ MIS-C በህፃናት ላይ ሊያመጣ ስለሚችለው ድንገተኛ የኩላሊት ተግባር መስተጓጎል ለማጥናት የተነሱት፡፡ ትኩሳት፣ ማቃጠልን እና የአንዳንድ የሰውነት አካላት ስራ ማቆምን (ኩላሊቶችን ጨምሮ) የሚያስከትለው MIS-C በኮቪድ-19 ሳብያ የሚመጣም ሊሆን ይችላል፡፡
አጥኚዎቹ ካለፈው ዓመት መጋቢት እስከ ነሃሴ ድረስ በአሜሪካኗ ኒው ዮርክ ከተማ በሚገኙ አራት ሆስፒታሎች ህክምናቸውን ሲከታተሉ የቆዩ 152 ታካሚዎችን ተመልክተዋል፡፡ በዚህም አፋጣኝ ህክምና የሚያስፈልገው ኮቪድ-19 ካለባቸው 97 ህፃናት መካከል ስምንቱ (8.2 በመቶው) የኩላሊት ጉዳቱ ታይቶባቸዋል፡፡ ሌሎች ተመሳሳይ ኮቪድ-19 ሁኔታ ያልተገኘባቸው 55 ህፃናት ደግሞ በሆስፒታል ቆይታቸው የ MIS-C ህክምናን ሲከታተሉ ነበር፡፡ ከነዚህ 55 ህፃናት ውስጥ አስሩ (18.2 በመቶው) የኩላሊት ጉዳት ታይቶባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ 11.8 በመቶ የሚሆኑት ታካሚዎች ድንገተኛ የኩላሊት ተግባር መስተጓጎል አስተናግደዋል፡፡ ታድያ የጤና ችግሩ ከሌሎቹ በተለየ ጥቁር ህፃናት ላይ በሦስት እጥፍ የበረታ ነበር፡፡ በተጨማሪም ከ152ቱ ህፃናት ውስጥ ሁለቱ ለሞት የተዳረጉ ሲሆን አንደኛው ይህ ድንገተኛ የኩላሊት ተግባር መስተጓጎል ተገኝቶበታል፡፡
ሆኖም አጥኚዎቹ ህፃናቱ ወደ ሆስፒታሉ ከመግባታቸው አስቀድሞ በኩላሊታቸው ላይ መስተጓጎል ይኑርባቸው አይኑርባቸው ማረጋገጥ አልቻሉም፤ ምርመራውም ሆስፒታል ውስጥ በነበሩበት ሰዓት ብቻ የተከናወነ የቤተ-ሙከራ ምርመራ ነው፡፡ ከህፃናቱ ውስጥ ግማሹ ሆስፒታል በገቡበት ሰዓት የህክምና እርዳታ የሚያሻው ኮቪድ-19ኝንም ሆነ የኩላሊት ጉዳቱን ያሳዩ ሲሆን 80 በመቶው MIS-C ያለባቸውም እንዲሁ የኩላሊት ጉዳቱ ተገኘኝቶባቸዋል፡፡
በተመሳሳይ ከኮቪድ-19 እና MIS-C ጋር የተገናኙ የኩላሊት ጉዳቶችን አስመልክቶ ሌሎች የህክምና ባለሙያዎችም ተፅዕንዖው ሊኖር እንደሚችል ቢጠቁሙም በበሽታው መያዛቸውን ተከትሎ ሆስፒታል በሚገቡት ህፃናት ላይ የሚታይበት መጠን ግን በዚህ ጥናት ከተቀመጠው ያነሰ እንደሚሆን ይነገራል፡፡ 




© The Scientist   













Short info

× Chat