askwala.com - \"የቲቢ በሽታ ይገኝባቸዋል ተብሎ ከሚታሰቡ 157 ሺህ ሰዎች 29 በመቶ ያህሉ ወደ ህክምና አልመጡም!\" የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ
Header







"የቲቢ በሽታ ይገኝባቸዋል ተብሎ ከሚታሰቡ 157 ሺህ ሰዎች 29 በመቶ ያህሉ ወደ ህክምና አልመጡም!" የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ


ለ15ኛ ጊዜ የሚካሄደው አመታዊ የቲቢ ምርምር ጉባኤና በዓለም ለ39ኛ በሀገራችን ለ24ኛ ጊዜ የሚከበረው የዓለም ቲቢ ቀን መድረክ “የቲቢ በሽታን ለመግታት ጊዜው አሁን ነው! “በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ነው፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ድጉማ በጉባኤው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር ምንም እንኳ በተሰሩ ስራዎች ከፍተኛ መሻሻል ቢኖርም አሁንም ሀገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ በቲቢ በሽታ እየተጠቁ ካሉ 30 ሀገራት አንዷ በመሆኗ ብዙ ስራዎች ይቀራሉ ብለዋል፡፡ በዓመት 157 ሺህ ሰዎች በቲቢ እንደሚያዙ ከእነዚህ መካከል 21 ሺህ ሰዎች በየዓመቱ እንደሚሞቱ የጠቆሙት ዶ/ር ደረጀ በሽታው እንደሚገኝባቸው ከሚታሰቡ ሰዎች 29 በመቶ ያህሉ ወደ ህክምና እንዳልመጡ ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም መድኃኒት የተላመደ ቲቢ ስርጭት መጨመሩን በሽታው እንደሚገኝባቸው ከሚታሰቡ ሰዎች መካከል መለየት የተቻለው 41 በመቶ ያህሉን መሆኑን ጠቅሰው በሽታውን ለመከላከል ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የውስጥ ደዌና የሳንባ ስፔሻሊስት ዶ/ር አምሳሉ በቀለ በበኩላቸው የቲቢና የኮሮና በሽታ ምልክቶች ተመሳሳይ በመሆናቸው ሳል ያለባቸው ሰዎች ኮሮና እንደያዛቸው በማሰብ በቤታቸው የመቆየት አዝማሚያ ማሳየታቸውን ገልፀው ሳል በተለይም 2 ሳምንትና ከዛ በላይ የቆየ ሳል ሲኖር ለቲቢ መመርመር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ በሚገኙ ከ4 ሺህ በላይ መንግስታዊና በተፈቀደላቸው ከ8 መቶ በላይ መንግስታዊ ባልሆኑ ጤና ተቋማት የቲቢ በሽታ ምርመራ፣ ህክምናና ክትትል አገልግሎት በ67 ጤና ተቋማት ደግሞ መድኃኒት የተላመደ ቲቢ ህክምና እንደሚሰጥ ከ3000 የማያንሱ የቲቢ መመርመሪያ ላቦራቶሪዎችም አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ መረጃ ያመለክታል፡፡ 

















Short info

× Chat