askwala.com - ምርጫና የሳይበር ደህንነት ስጋቶች
Header







ምርጫና የሳይበር ደህንነት ስጋቶች


በዓለማችን ቁጥራቸው ትንሽ የማይባሉ ሀገራት በተለያዩ ጊዚያቶች ባካሄዱት ሀገራዊ ምርጫ የተለያዩ የሳይበር ደህንነት ሥጋቶች አጋጥሟቸዋል፡፡ ለአብነት የሳይበር ደህንነት ጉዳይ በምርጫ ሂደት ላይ በሰፊው ውዝግብ ያስነሳው እና ዓለም አቀፍ ትኩረት ያገኘው በፈረንጆቹ 2016 የተካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ የጋጠመውን የሳይበር ጥቃት ተከትሎ ነው፡፡
ይህ አጋጣሚ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሳይበር ደህንነትን ማረጋገጥ የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ እንዲሆን ከማድረጉም ባለፈ የዲሞክራሲ ሥርዓታቸው በዳበረም ይሁን ባልዳበረ ሀገራት ላይ የሳይበር ደህንነት ስጋት ትኩረት እንዲያገኝ ማድረግ አድርጎ ነበር፡፡
ሀገራዊ ምርጫ ህገ-መንግስትንና የተለያዩ መመሪያዎችን መሠረት በማድረግ እና በቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚከናወን ነው፡፡ ይህ ማለት እንከን አልባ መመሪያ ወይም ከሳይበር ጥቃት ኢላማ ውጪ የሚሆን ቴክኖሎጂ ይኖራል ማለት አይደለም፡፡ በምርጫ ወቅት ከባዱ ፈተናም ከተለያዩ አካላት የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶችንና ተግዳሮቶችን በተዓማኒነት፣ በኦዲት እና በመቆጣጠሪያ ዘዴዎች መከታተልና እና መፍትሔ መስጠት መቻል ነው፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ በተለምዶ የተሳሳቱ የሳይበር ደህንነት እሳቤ መካከል አንዱ የኤሌክትሮኒክስ ምርጫ የሚያካሂዱ ሀገራት ወይም ከፍተኛ የምርጫ ፕሮፋይል ማስቀመጫ ቴክኖሎጂዎች ብቻ ለሳይበር ጥቃት ሊጋለጡ እንደሚችሉ ማሰብ ነው፡፡ ነገር ግን ሁሉም ምርጫዎች ከመራጮች ምዝገባ እስከ የምርጫ አስፈጻሚ አካል ድረ-ገጽን ድረስ በኢንፎርሜሽን እና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይ.ሲ.ቲ.) መሳሪያዎች ላይ የተመረኮዙ ናቸው፡፡
የሳይበር ጥቃቶቹ ዓይነት፣ ተቀናቃኞች እና የሳይበር ጥቃት መፈጸሚያ መንገዶች ከሀገራት ሀገራት ይለያያሉ፡፡ ከምርጫ አስፈጻሚ አካል በተጨማሪ ከፍተኛ ሥልጣን ደረጃ ላይ የሚገኙ አካላት፣ የደህንነትና የዲሞክራሲ ተቋማት አሁን ላይ አዲሱ ቴክኖሎጂ በዲሞክራሲ ሂደትና ምርጫ ላይ እያሳረፈ ያለውን አደጋ አስቀድሞ በመረዳት፣ በመከላከል እና በመፍታት ላይ የበለጠ ተቀናጅተው ሊሠሩ ይገባል፡፡
ሁለተኛው የተሳሳተ እሳቤ ምርጫ አስፈጻሚው አካልን በምርጫው ሂደት ለሚያጋጥሙ የሳይበር ደህንነት ስጋቶች ዋነኛው ተጠያቂ አድርጎ መውሰድ ነው፡፡ ነገር ግን በምርጫ እና በዲሞክራሲ ሂደት ውስጥ የሳይበር ጥቃቶች የሚከሰቱት ብዙ ተዋንያን ለመቆጣጠር ጥረት የሚያደርጉበት በመሆኑ ነው፡፡ እነዚህም፡-
• ከምርጫ ጋር ግንኙነት ባላቸው መሠረተ-ልማቶች ላይ የሳይበር ጥቃቶችን በመፈፀም እና መረጃዎች እንዲያፈተልኩ በማድረግ በምርጫው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና መረጃ አያያዝ ላይ የምስጢራዊነት፣ የተዓማኒነት እና የተደራሽነት ቅቡልነቱን እንዲያጣ ማድረግ፤
• የምርጫ አስፈፃሚውን እና የዴሞክራሲ ተቋማቱን ተዓማኒነት ለማሳጣት የሐሰት መረጃ ዘመቻዎችን ማካሄድ፤
• ከምርጫ ጋር ግንኙነት ባላቸው ባለድርሻ አካላት፣ ፓርቲዎች፣ እጩ ተወዳዳሪዎች፣ ሚዲያዎች እና ቅስቀሳዎች ላይ የሳይበር ጥቃቶችን መፈፀም፤
• የፖለቲካ ክርክሩን ሂደት በሚፈልጉት አቅጣጫ ለማስያዝ የሚሰራጩ የሀሰት መረጃ ዘመቻ ማካሄድ ዋነኛ ፈተናዎች ናቸው፡፡
እነዚህን የሳይበር ደህንነት ስጋቶች ለመቆጣጠር በመደበኛ መንገድ በምርጫ አስፈጻሚው አካል ከሚወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎች ባለፈ የተለያዩ አካላትን የተቀናጀ ትብብር እና ሥራ ይጠይቃል፡፡ ይህም ግብዓትንና የሰው ኃይልን ከማቀናጀት ባለፈ ከሀገር ውስጥም ይሁን ከውጭ በምርጫው ሂደት ላይ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል ሁሉንም አቀፍ ትብብርና ቅንጅት ያስፈልጋል፡፡
በተለይ በከፊልም ሆነ በሙሉ ከሳይበር ምህዳር ጋር የተገናኙ የምርጫ ሁነቶች የተለያዩ ኢላማ ባነገቡ የዉስጥም ሆነ የዉጭ አካላት ዒላማ ዉስጥ መግባታቸዉ ስለማይቀር ሉዓላዊነትን እስከ ማሳጣት ድረስ የሚደርሱ የሳይበር ጥቃት ሊከሰቱ የሚችሉ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። 

















Short info

× Chat