askwala.com - የሰው ደም እና ሽንትን በመጠቀም ማርስ ላይ ቤት መስራት ይቻላል ተባለ
Header







የሰው ደም እና ሽንትን በመጠቀም ማርስ ላይ ቤት መስራት ይቻላል ተባለ


የማንቼስተር ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የማርስን አፈር ወደፊት በፕላኔቷ ላይ ሊሰሩ ለሚታሰቡ ህንፃዎች ብቁ ያደርግ ዘንድ የሰው ልጅ ደም፣ ሽንት፣ ላብ ብሎም እንባን ከማርስ ወይም ጨረቃ አቧራ ጋር ማዋሀድ እንደሚቻል ገለፁ፡፡ ውህዱ ልክ እንደ ተለምዶው አርማታ ሁሉ በ3ዲ ቴክኖሎጂ ወይም በሌላ አማካኝነት ለየሚገነቡ ህንፃዎች ግብዓት የሚሆን ጠንካራ ማጣበቂያን ሊሰጥ እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ ይህም በሌላ አነነጋገር ወደ ስፍራው የሚያመሩ የህዋ ተመራማሪዎች ቤታቸውን በራሳቸው ደም፣ ሽንት፣ ላብ እና እንባ መገንባት አለባቸው እንደማለት ነው፡፡
ተመራማሪዎች እንከዛሬ ድረስ በማርስ ላይ አርማታ መሰል ነገርን መስጠት የሚችል ጠንካራ ቴክኖሎጂን ይዘው ለመምጣት ሲጥሩ መቆየታቸውን የሚያወሱት የጥናቱ ተሳታፊ አለድ ሮበርትስ መልሱ ከራሳችን ሰውነት ሊወጣ መቻሉን ግን ብዙም አስበነው እንደማናውቅ ይጠቅሳሉ፡፡ በጥናቱ ላይ እንደተቀመጠውም እንደ ኢን ቪኖ ባይንደር ያሉ በሰው ልጅ ደም ውስጥ የሚገኙትን ለየት ያሉ ፕሮቲኖችን በመጠቀም የማርስን አፈር ወደ አርማታነት መቀየር ይቻላል፡፡ ከሽንት የሚገኘው በናይትሮጅን የተሞላ ግብዓት በበኩሉ ይህን ቁስ ይበልጥ የሚያጠነክረው ይሆናል፡፡
ተመራማሪዎቹ “አስትሮክሪት” ብለው የሰየሙትን ይህን አርማታ በመጠቀም ህንፃውን በ3ዲ ህትመት አማካኝነት በማርስ ምድር ላይ መስራት እንደሚቻል ጠቅሰዋል፡፡ እንደ ተመራማሪዎቹ ከሆነ አስትሮክሪት ከተለምዶው አርማታ የሚስተካከል ጫናን የመቋቋም ጥንካሬ ያለው ነው፡፡ ታድያ በስሌታቸው መሰረት 6 የህዋ ተመራማሪዎች በሁለት ዓመታት የማርስ ቆይታቸው ብቻ 500 ኪ.ግ የሚመዝን ግብዓትን መስጠት የሚችሉ ሲሆን ይህም ወደ ስፍራው ለሚያመሩ ተጨማሪ የህዋ ተመራማሪዎች መኖርያ ሊሆን የሚችል ቤትን ማቆም ይችላል፡፡
ተመራማሪዎች በማርስ ላይ ህንፃን ለመገንባት የሚያስችል ለየት ያለ ሀሳብ ይዘው ሲመጡ ይህ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ተመራማሪዎች ከምድር ውጪ ባሉት ስፍራዎች ላይ እንደ ሽንት እና እንጉዳይ ያሉ ግብዓቶችን ለግንባታ የመጠቀም ሀሳብን ሲያንሸራሽሩ ነበር፡፡
ደምን ለማጣበቂያነት መጠቀሙም ቢሆን አዲስ ግኝት አይደለም፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለይም በመካከለኛው ዘመን የደም ፕሮቲኖች ባላቸው የማጣበቅ አቅም ሳብያ የሰው ልጆች የእንስሳትን ደም ለማጣበቂያነት ተጠቅመው ህንፃ ሲገነቡ ቆይተዋል፡፡ 




© Futurism   













Short info

× Chat