askwala.com - የሳይበር ደህንነት የሚጠበቅባቸው ሦስቱ መሠረታዊ ነገሮች ምንድን ናቸው?
Header







የሳይበር ደህንነት የሚጠበቅባቸው ሦስቱ መሠረታዊ ነገሮች ምንድን ናቸው?

Image name: Confidentiality_Integrity_Availability.jpg

ምሉዕነት፣ ምስጢራዊነት እና ተደራሽነት መሠረታዊ የሳይበር ደህንነት መጠበቂያ መሠረቶች ናቸው፡፡ ማናቸውም የደህንነት መቆጣጠሪያ እና የደህንነት ሥጋቶች መነሻ ከእነዚህ በአንዱ ወይም በሦስቱ ፅንሰ-ሀሳቦች በመነሳት የሚፈጠር ነው፡፡ በመሆኑም የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ እና የተሟላ ለማድረግ ቀጥለው የቀረቡትን ሦስቱ መሠረታዊ የደህንነት ማስጠበቂያ ጉዳዮች ትኩረት ልንሰጣቸው ይገባል፡፡
1. ምስጢራዊነት (Confidentiality)፡- ምስጢራዊነት ማለት ዳታን (data)፣ ቁስን (objects) ወይም ሀብትን (resources) ፈቃድ ከሌለው ሰው ወይም በርባሪ መሰወር ወይም መመስጠር ማለት ነው፡፡ ይህም ምስጢራዊ መረጃ ላልተገባ ሰው ወይም እውቅና እና ፈቃድ የሌለው ሰው እንዳይጠቀመው የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡
ለምሣሌ የቢዝነስ ተቋማት ተፎካካሪዎቻቸው እንዲያውቁባቸው የማይፈልጓቸውን ሥራዎች እና አሠራሮች ወይም የአንድን ተቋም ሠራተኞች ደንበኞች ግላዊ መረጃ ተላልፎ ላልተገባ ወይም ፈቃድ ለሌለው አካል እንዳይደርስ መጠበቅ ማለት ነው፡፡
2. ምሉዕነት (Integrity)፡- ምሉዕነት ማለት መረጃዎች ፈቃድ በሌላቸው አካላት እጅ ሳይገባ ተዓማኒነት እና ትክክለኛነቱን ጠብቆ እንዲገኝ ማድረግ ነው፡፡ ይህም አንድ መረጃ ፈቃድ በሌለው አካል እንዳይቀየር መጠበቅ እና ማረጋገጫ መስጠት ማለት ነው፡፡
ለምሣሌ በሲስተም /system/ ውስጥ የተከማቸውን መረጃ ወይም በሥርዓት ውስጥ የሚተላለፉ እንደኢሜይል ያሉ መረጃዎችን ትክክለኝነታቸው ተረጋግጦ እንዲጠበቅ እና በተሟላ ሁኔታ ወደተፈለገው አካል እንዲደርሱ የማስቻል ሂደት ነው፡፡
3. ተደራሽነት (Availability)፡- ተደራሽነት ማለት ፈቃድ ያለቸው ተጠቃሚዎች ሲስተሙን ወይም የፈለጉትን ሀብት ያለምንም ችግር እንዲጠቀሙ ማስቻል ነው፡፡ መረጃ ሥርዓት ጠቀሜታ የሚኖረው ፈቃድ ላለው አካል መረጃው በተገቢ ሁኔታ ተደራሽ ማድረግ ሲቻል ነው፡፡ በመሆኑም መረጃው በሚፈልገው ጊዜ ያለአንዳች ችግር ማግኘት ሲቻል የመረጃው ደህንነት ተጠብቋል እንላለን፡፡
ለምሣሌ የድረ-ገጻችን ተደራሽነት እና ምላሽ ሰጪነት ማረጋገጥ በቢዝነስ ሥራ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ቢቀርና ለአጭር ጊዜ እንኳ የሚቋረጥ የአንድ ድርጅት የድረ-ገፅ አገልግሎት ከፍተኛ ኪሳራ በድረጅቱ ላይ ሊያስከትል የሚችል፣ ደንበኞች በድርጅቱ ላይ ያለቸውን ደስተኝነት የሚቀንስ እና ድርጅቱ የነበረውን መልካም ስም የሚያበላሽ ሊሆን ይችላል፡፡ 

















Short info

× Chat