ፅንሰ ሐሳቡ አዲስ የበይነ መረብ መቼትን በመፍጠር ሰዎች በኢንተርኔት አማካኝነት የሚያገኟቸውን አገልግሎቶች ከመመልከት ባሻገር በመሣሪያዎች አማካኝነት ወደ ምናባዊው ዓለም ተሸጋግረው ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል ያቀደ ነው፡፡
ኢንቴክ ኦፕን በተሰኘው ድረ-ገፅ ትንተና መሰረት ይህን ምናባዊ ዓለም ለመገንባት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አበርክቶ ጉልህ ነው፡፡
ሐሳቡ ሰዎች ቦታ፣ ጊዜ እና ሁኔታዎች ሳይወስኗቸው የምናባዊ ዓለም ተሳታፊ በመሆን ስራ የሚሰሩበት፣ እርስ በርስ የሚገናኙበት እና ጨዋታዎችን በጋራ የሚጫወቱበት የበይነ መረብ ምናባዊ ከባቢን የመፍጠር የመጪው ጊዜ ተጠባቂ እውነታ ነው፡፡
ሜታቨርስ የሚለው ቃል አሁን ላይ በቴክኖሎጂው ዓለም አነጋጋሪ እየሆነ ይገኛል፡፡ ቃሉን በመሰየም በሳይንሳዊ ልብወለድ ጽሁፎቹ የሚታወቀው አሜሪካዊ ኒል ስቴፈንሰን ቀዳሚ ነው፡፡
ደራሲው በ1992 (እ.ኤ.አ) ባሳተመው ስኖው ክራሽ በተሰኘ ልብወለድ መጽሐፉ የእውነተኛ ሰዎች አምሳያ የሆኑ (Avatars) የምናባዊው ዓለም ነዋሪዎች የሚገኙበት ባለሶስት ልኬት (3D) ምናባዊ ዓለምን ለመግለጽ ተጠቅሞበታል፡፡