በዕለት ከዕለት ሕይወታችን የምንጠቀማቸው እና ከኢንተርኔት ጋር ግንኙነት ያላቸው ስማርት ስልኮች፣ የቤት እና የቢሮ መገልገያዎች፣ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ማሽኖች፣ የሕክምና መሣሪያዎች፣ ተለባሽ ቁሶች እና የመሳሰሉትን የኢንተርኔት ቁሶች ብለን እንጠራቸዋለን፡፡
በስታቲስታ መረጃ መሠረት በአውሮፓውያኑ 2020 በዓለም ዙሪያ የበይነመረብ ትስስር ያላቸው ቁሶች ብዛት 8.74 ቢሊዮን ነው፡፡ በድረ-ገፁ ትንበያ መሠረት ይህ ቁጥር በአውሮፓውያኑ 2030 ሀያ አምስት ቢሊዮን እንደሚሻገር ይጠበቃል፡፡
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና የኢንተርኔት ቁሶች መጣመር ደግሞ አስተውሎት የተላበሱ ማሽኖች እንዲፈጠሩ አስችሏል፡፡ ይህም ማለት ቁሶቹ ሙሉ በሙሉ በራሳቸው ወይም በአነስተኛ የሰው ልጅ ጣልቃ ገብነት ውሳኔዎችን እንዲወስኑ አስችሏቸዋል፡፡ ከዚህም አለፍ ሲል ቁሶቹ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አማካኝነት በሂደት ከዳታ እንዲማሩ በማድረግ እራሳቸውን እያሻሻሉ እንዲመጡ ያግዛቸዋል፡፡