ግለሰቡ በዋስትና ወጥቶ ነበር ተብሎ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች እየተሰራጨ ያለው መረጃም ሀሰተኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡
እስካሁን በፖሊስ እና የዐቃቤ ሕግ የምርመራ ቡድን እስካሁን በተሰበሰበው ማስረጃ መሰረት ተጠርጣሪው ሚካዔል ሽመልስ ሟች አዳናዊት ይሄይስ ላይ ከ10 ዓመቷ ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ሲፈጽምባት እንደቆየ እና ሟች እድሜዋ 17 ዓመት እስኪደርስም ድረስ ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈጽምባት ቆይቶ መስከረም 14 ቀን 2015 ዓ.ም ድርጊቱን ሲፈጽም ያየው ሰው ለእናቷ በተናገረው መሰረት ጥቆማው ለፖሊስ ይደርሳል፡፡
ፖሊስም በአስገድዶ መድፈር ወንጀል የጠረጠረውን ይህንኑ ግለሰብ ለመያዝ እንዲችል ከፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ በማውጣት ወደ መኖሪያ ቤቱ ይሄዳል፡፡ ይሁንና ተጠርጣሪው የፖሊሶችን መምጣት ያውቅ ነበርና አስቀድሞ ከአካባቢው ይርቃል፤ በዚህም ምክንያት ፖሊስ ወደ መጣበት ተመልሶ በሌላ መንገድ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት ማድረጉን ይቀጥላል፡፡
ከሰዓታት በኋላ ተጠርጣሪው ከሄደበት ተመልሶ ሟች ከእናቷ ጋር እንዳለች “ለፖሊስ የጠቆምሽው እና ያዋረድሽኝ አንቺ ነሽ” በማለት በስለት ወግቶ እንደገደላት እና ወደ ቤቱ ተመልሶ ልብሱን በመቀየር ሊያመልጥ ሲል በአካባቢው ህብረተሰብ ሊያዝ እንደቻለ ያስረዳል፡፡
ፖሊስ እና በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በአሁኑ ጊዜ ምርመራቸውን በማጠናቀቅ ክስ መስርቶ በህግ ለማስጠየቅ በሚያስችል ሁኔታ በጥንቃቄ እየሰሩ ያለ ሲሆን ግለሰቡ ሟችን የገደላት በዋስትና ከወጣ በኋላ ነው በሚል እየተሰራጨ ያለው መረጃ ሀሰተኛ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
በቀጣይ የምርመራ ሂደቱን ተከታትለን መረጃ የምናቀብል መሆኑን እንገልጻለን፡፡