askwala.com - የራንሰምዌርን ጥቃት ምንነት እና የመከላከያ መንገዶች
Header







የራንሰምዌርን ጥቃት ምንነት እና የመከላከያ መንገዶች


አጥፊ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም መረጃን መስጥሮ የመያዝ እና የማገት እንቅስቃሴ ባለፉት ጥቂት አመታት ውጤታማ የጥቃት መፈጸሚያ መንገድ እየሆነ መጥቷል፡፡

የዚህ ሶፍትዌር ዓላማ ጥቃት ተፈጽሞ መረጃቸው የተመሰጠረባቸው አካላትን መረጃዎቻቸው ወደነበሩበት ቦታ ማስመለሻ የገንዘብ ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚያስገድድ ነው፡፡

ራንሰምዌር ጥቃት /Ransomware/ እንደሌሎች የኮምፒውተር ቫይረሶች ሁሉ የደህንነት ክፍተት ቀዳዳ በመፈለግ ወይም ተጠቃሚው አካል ተጋላጭነት ያለው ሶፍትዌር በኮምፒውተሩ ላይ እንዲጭን በማድረግ የሚፈጸም የጥቃት ዓይነት ነው፡፡

የራንሰምዌር ጥቃትን ለመከላከል ሊተገበሩ የሚገቡ ወይም መደረግ የሌለባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

1. ለእገታ ማስመለሻ ክፍያ በፍጹም አለመፈጸም፡፡ ክፍያ መፈጸም የሚጠቅመው እና የሚያበረታታው አጥቂዎችን ነው፡፡ በመሆኑም የእገታ ማስለቀቂያው ገንዘብ ከተከፈለ በኋላም መረጃውን መልሰን ስለማግኘታችን ምንም ማስተማመኛም ባለመኖሩለ እገታ ማስመለሻ ክፍያ መፈጸሙ አይመከርም ፡፡

2. የትኛውም ፋይል ሲጠቃ አስቀድመው ከያዙት አስተማማኝ መጠባበቂያ በመውሰድ መጠቀም፡፡ ከመጠባበቂያ መያዣ ፋይልን መልሶ ወደሥራ ማስገባት ፈጣኑ እና ውጤታማው ወደሥራ መመለሻ መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ በየጊዜው ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ መጠባበቂያ(back up) የመያዝ ልማዳችንን ማዳበር አስፈላጊ ነው፡፡

3. በፍፁም በኢ-ሜይል ለሚላኩ የማይታወቁ መልዕክቶች፣ የማናውቃቸው የስልክ ጥሪዎች እና የጽሑፍ መልዕክቶች እንዲሁም ግላዊ መረጃን አሳልፎ አለመስጠት፡፡ የፊሺንግ ጥቃት ፈጻሚዎች ሠራተኞች አጥፊ ሶፍትዌሮችን እንዲጭኑ ሊያታልሉ ወይም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) ዲፓርትመንት አካል እንደሆኑ በመግለጽ ሊያታልሉን ስለሚሞክሩ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

4. አስተማማኝ ጸረ-ቫይረስ ሶፍትዌር እና ፋየርዎል /firewall/ ይጠቀሙ፡፡ ጠንካራ ፋየርዎል መገንባት እና የደህንነት መጠበቂያ ሶፍትዌሮችን ወቅታዊ ዝመና ማድረግ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡

5. የይዘት ማጣሪያ እና መለያን ለመልዕክት መቀበያ ሰርቨሮ (Mail Server) ይጠቀሙ፡፡ ወደ ሰርቨሩ የሚገቡ መልዕክቶችን በሙሉ ስጋት እንዳይኖራቸው ስካን /scan/ ሊደረጉ እና አስጊ የሚመስሉ ፋይሎች ካሉ ሊታገዱ ይገባል፡፡

6. ሁሉም ሥርዓቶች እና ሶፍትዌሮች ወቅታዊ የክፍተት መሙያ ዝመና የተደረገላቸው መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ጠለፋ የተደረገባቸው ገጾች አብዛኛውን ጊዜ አጥፊ ሶፍትዌር ለማሰራጨት ይውላሉ በመሆኑም ጥቃትን ለመከላከል ተጋላጭነት ባላቸው ሶፍትዌሮች ላይ ወቅታዊ የክፍተት መሙያ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

7. የህዝብ ዋይፋይ ከመጠቀም መቆጠብ፡፡
የራንሰምዌር ጥቃትን ለመከላከል ሊተገበሩ ከሚገባቸው አንኳር ጉዳዮች ውስጥ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ 

















Short info

× Chat