በመድረኩ ላይ የጤና ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ በጥናቱ ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች እና የህፃናቱ ወላጆች ተገኝተዋል። ጥናቱ በዋናነት ትኩረት ያደረገው አዲስ የተዘጋጀው የህፃናት ፕሪማኩዊን እንክብል ያለውን ስር-ነቀል ፈዋሽነት መገምገም ላይ ነው።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ሶንቆ እንደገለጹት፤ የወባ በሽታ በክልሉ ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና እያደረሰ ይገኛል። እስካሁን ወላጆች ለህፃናት የሚሆን በቂ ዝግጅት ባለመኖሩ የአዋቂዎችን እንክብል በመስበር እንደሚሰጡ ጠቁመው፤ ይህም ለተሳሳተ የመድኃኒት መጠን (ከመጠን በላይ ወይም በታች) እና ለመድኃኒቱ መራራነት ምክንያት በመሆን ህክምናውን አስቸጋሪ አድርጎት መቆየቱን አስረድተዋል።
በመድረኩ ላይ የቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፎች እንደሚያመለክቱት፣ የወባ በሽታ ከጤና ቀውስ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ጫና ፤ ወላጆች ልጆቻቸው በወባ ሲያዙ እነሱን ለማስታመም ሲሉ ከመደበኛ ስራቸው ይስተጓጎላሉ። ይህም በውጤታማነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በማሳደር የቤተሰብን ገቢ ይቀንሳል። እንዲሁም ማህበራዊ ጫና፤ በሽታው በህፃናት ላይ በሚያደርሰው የጤና መቃወስ ምክንያት ተደጋጋሚ ከትምህርት መቅረት የሚያስከትል ሲሆን፣ ይህም በረጅም ጊዜ የህፃናቱን የትምህርት ውጤትና የእውቀት እድገት ይገታል። በከባድ የወባ በሽታ የሚያዙ ህፃናት ደግሞ ለዘላቂ የአካል ወይም የነርቭ ጉዳት ሊዳረጉ እንደሚችሉ በጥናቱ ተመላክቷል።
በአርባ ምንጭ ድል ፋና ሆስፒታል የጥናቱ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ከበደ አልማው በበኩላቸው፤ አዲሱ የህፃናት እንክብል ልጆች በሚወዱት ጣዕም እና በቀላሉ መውሰድ በሚችሉበት መጠን እንዲዘጋጅ ታስቦ የተጠና መሆኑን ገልጸዋል። ይህ መሆኑ ወላጆች መድኃኒቱን ለመስጠት የሚቸገሩበትን ማህበራዊ ጫና የሚቀንስና ህፃናቱ በፍጥነት አገግመው ወደ ትምህርታቸው፣ ወላጆችም ወደ ስራቸው እንዲመለሱ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።
የጥናቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር እንዳለማው ጋዲሳ በመዝጊያ ንግግራቸው፤ ወባን ለመከላከል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን አሳስበው፣ ለጥናቱ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉ ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል።